ወቅታዊ መልዕክት ለመምህራንና ኢንቬስተሮች
ይሄይስ አእምሮ
በጣም
አሳሳቢ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትንሽ መናገር አሰኘኝ፡፡ ሀተታ ሳላበዛ ባጭር ባጭሩ ላስቀምጥ፡፡
ይሄን
ሰሞን ልጆቼ እቤታቸው መዋል ጀምረዋል፡፡ ለምን ስላቸው መምህራን ደመወዝ ካልተጨመረልን ብለው በማመጻቸው ክፍል እንደማይገቡና
ከናካቴውም የማይመጡ እንዳሉ ነገሩኝ፡፡ ይሄን ነገር ሳጠያይቅ በአዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በዚሁ የደመወዝ ጭማሪ ሳቢያ በብዙ
ትምህርት ቤቶች ትምህርት መቆሙን ተረዳሁ፡፡ ‹እኔም ባንዴ አልተቆመጥኩም› አለች አሉ አንዷ- ጣቶቿን ማሳከክ የጀመራት ሕጻን
ልጇ ስለማሳከኩ ለእናቷ ስትነግራት፡፡ አንድ በሉ፡፡
መንግሥት
የደመወዝ ጭማሪ አደረግሁ ብሎ በነፍስ ወከፍ አምሳና ስልሳ ብር መጨመሩ እንደትልቅ ዜና ተቆጥሮ በሚዲያ ተወራ፡፡ ያንን
ተከትሎም ይሄ መደዴ ነጋዴና ቤት አከራይ ሁላ የሸቀጡን ዋጋና
የቤቱን ኪራይ ሽቅብ አጓነው፡፡ አንዲት መምህር ብሶቷን ስትናገር እንደሰማሁት፤ ‹ መንግሥት የአምሳ ብር ማስተካከያም ይበሉት
ጭማሪ ባደረገልኝ ማግሥት ቤት አከራዮቼ ወርሃዊ ኪራዩን ከአራት መቶ አምሳ ወደ አምስት መቶ አምሳ አወጡብኝ፡፡ ታዲያ በዚህ
ሁኔታ እንዴት መኖር እችላለሁ? ጭማሪ ተብዬው ይብስ ጎዳኝ እንጂ ምን ጠቀመኝ? በዚህ ሁኔታ ሠራሁ አልሠራሁ ምን ዋጋ አለው?
ከዚህ ኑሮ ሞት አይሻልም?›ብላለች፡፡ ትክክል ናት፡፡ ሰዉ አቅል አጥቷል፡፡ በገንዘብ ፍቅርም ጭንቅላቱ ናውዟል፡፡ ዛሬ ማታ
በሚዲያ ጭማሪ ቢጤ ትታወጅ - የጭማሪውን መጠንና ለማን እንደተጨመረም ሳያጤኑ ነጋዴዎችና አከራዮች ወዲያውኑ ማግሥቱንም እንኳን
ሳይጠብቁ በደንበኛቸው ላይ የዋጋ ቁልል ይከምራሉ፡፡ አንጎል እሚባል ነገር የፈጠረባቸውም አይመስሉ፡፡ እንደወያኔ ዓሣሞች
ናቸው፡፡ እንደቀዳዳ በርሜል ሆዳቸው የማይሞላ እምብርት የለሾች፡፡
የሰሞኑ
የእህል ዋጋ አይነሳ፡፡ በ1300 ብር ሂሳብ ሃምሳ ኪሎ ድብን ያለ ጥቁር ጤፍ ገዝታ ስትመጣና መርዶውን ስትነግረኝ ስለለመድሁት
ምንም አላልሁም - ባለቤቴ፡፡ አልኳትም ‹እኛስ ስለቻልን ጥቁሩንም ቢሆን ገዛን፤ ከኛ ያነሰ ገቢ ያላቸው እንዴት ሊሆኑ ነው?›
ምን ትመልስልኝ? የሁሉም ነገር ዋጋ ማሻቀብ እንጂ መቀነስ ብሎ ነገር የለም፡፡ ቲማቲም እንኳን ኪሎው 15 ብር ሲገባ? ነጭ
ማኛ ጤፍማ እንደሚባለው 1600ን አልፏል አሉ፡፡ ኢትዮጵያም እንደአሥመራ ሆነች፡፡ እነሱ እንኳን አሾልኮ የሚሰጣቸው ዘመድ
አያጡም፡፡ ካለው ተወለድ ወይ ካለው ተጠጋ ነው ነገሩ፡፡ለማንኛውም ሁለት በሉ፡፡
ባለፈው
ሰሞን አንድ መጣጥፌ ላይ ቀደም ባለ ወቅት በአንድ የጠበል ሥፍራ የታዘብኩትን ነገር አስታውሼ መጠቆሜ ይታወሳል፡፡
በቅርቡ
ደግሞ አንድ ተዓምር በከተማው ሲወራ ሰምቼ በዐይኔ አይቼ ለማረጋገጥ ፈለግሁና ወደቦታው አመራሁ፡፡ ጉድ ተመልከቼ መጣሁ፡፡
የመታችና የአስመታች ጀምበር እየጠለቀች መሆንዋንም ታዘብኩ፡፡ ለቁሣካላውያን ሳይሆን እንደኔ ለሆናችሁ ሃይማኖታውያን ይህን
አስደናቂ ነገር ላውጋችሁ፡፡ ገና ባትሰሙትም ሦስት በሉ፡፡
ሥፍራው
ሞጆ አካባቢ ነው፡፡ ከተማዋ መግቢያ ደርሳችሁ ወደ ናዝሬት አቅጣጫ ስትጓዙ በስተቀኝ በኩል የሚገኘውን ፒስታ መገንጠያ ትይዙና
አስቸጋሪውን የገጠር መንገድ ለስድስት ኪሎ ሜትሮች ያህል ወደ ውስጥ ትገቡና ታገኙታላችሁ - ይህን የተዓምር ቦታ፡፡ የሕዝብ
ትራንስፖርት እንደልብ ነው - ዕድሜ ለአሥር ብራችሁ፡፡
በዚያ
ሥፍራ ማን አለ? በዚያ የተባረከና የተቀደሰ ሥፍራ አንድ ሰንሰለት የታጠቁ ከቁምጣና ከመቁጠሪያ እንዲሁም ከጸሎት መጽሐፍና
ከመስቀል በስተቀር ምንም ነገር ያልያዙ የእግዚአብሔር ባሪያ ወይም አገልጋይ ታገኛላችሁ፡፡ በትልቅ ሸለቆ ውስጥም እኚሁ አባት
በጸሎታቸው ፈውስ ይሰጡበት ዘንድ ፈጣሪ ያፈለቃቸውና በአርባ አራቱም ታቦታት ስያሜ የሚጠሩ በርካታ ጸበሎች ይገኛሉ፡፡ እኔ
በሄድኩበት ዕለት የተጠማቂው ቁጥር የቅንጅት የሚያዚያ 30/97 ዓ.ምን ሠልፍ ይመስላል፡፡ ሰው ቢጠፋህ አታገኘውም - በማጉሊያ
ካላስነገርህ፡፡ በላስቲክ አዳራሾችና ትናንሽ የላስቲክ ቤቶች እዚያው ከትሞ የሚጸለይለትና የሚጠበለው ሕዝብ ብዛት
ያስደነግጣችኋል - የከተሞችና የገጠሮች ሕዝብ ተነቅሎ እዚሁ ቦታ የሠፈረ ነው እሚመስል፡፡ በተለያዩ አጋንንታዊ ደዌያት
ተለክፈው እስኪፈወሱ ድረስ በጠበሉ ዙሪያ የሚኖሩት ዜጎች በጥቂቱ ከ10 ሺህ አያንሱም፡፡
በጸሎትና
በጠበል መርጫው ወቅት የሚነሳውን የአጋንንት ጩኸትና ያዙኝ ልቀቁኝ ፣ ጉሪያና መንበልበል ስትመለከቱ ምድር ላይ ሳይሆን ሲዖል
ውስጥ ያላችሁ ይመስላችኋል፡፡ ያን ሁሉ የሚለፈልፍና የሚጮህ ሰው ስታዩ እኛ ኢትዮጵያውያን በአብዛው ጊዜያችንን የምናውለው እርስ
በርስ ስንተባተብ እንደሆነ ብትጠረጥሩ አይፈረድባሁም፡፡ አንዱ ባንዱ ላይ ሲውልበትና ሲሰላለብ በሥራ ጥረታችን ወርቃማ
ልናደርገው ይችል የነበረውን ዘመን በከንቱ እያሳለፍን ነው፡፡ ለዚህ ከአንድ ጥቢኛ ለማታልፍ ትንሽዬ ለቆታ - ለዚች በጨጓራና
በልዩ ልዩ የውስጥ ደዌ ለተያዘች ሆድ ይህን ያህል ርቀት ተጉዘን በሰው ላይ ስናስመትትና ስንመትት ዕድሜያችንን በከንቱ
ፈጀን፡፡ (አንድ ጅብ በቀያችሁ ጧት በድንገት በሆነ ምክንያት ይሙት እንበል፤ በአንድ ሰዓት ውስጥ የሠፈሩ ነዋሪ ይቃረጠውና
ከሰዓት ፈርሱና አንዳንድ ነገሮቹ ብቻ ናቸው የሚቀሩት፡፡ ለምን? እግሩ ለመስለብ፤ ቅንድቡ ለቡዳ፤ ቆዳው ለዚህና ለዚያ
እየተባለ በሽሚያ ተወስዶ ቤት ውስጥ ይቀበራላ! አንገርምም? በድንቅ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ የምንገኝ ሕዝብ!)
በዚያ
ሥፍራ ምን ይደረጋል? በዚህ የተለዬ ሥፍራ የማይታይ ተዓምር የለም፡፡ በመጀመሪያ እግሬን ወደዚያ ቦታ ከማንሳቴ በፊት አንድ
የሰማሁት ነገር ነበር፡፡ አንድ በቅርብ የማውቀው ነጋዴ እቤቱ ውስጥ በብረት ታስሮ እንደሚጠበቅ ለዚያ ያበቃውም ባሠራው መተት
ምክንያት እንደሆነ ሰማሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- በዚህ ሰው ቤት አጠገብ አንድ ዶክተር ነበር፡፡ ይህ ዶክተር ፎቅ ቤት
ይሠራል፡፡ ይህ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት አንጻር ስሙን እዚህ ላይ የማላነሳው ወዳጄ(አሁን ወዳጄ አይሁንና) በምቀኝነት ተነሳስቶ(አሉኝ)
በመተት ያስገድለዋል፡፡ ቀደም ሲል ነው ይህ የሆነው እንግዲህ፡፡ የዚያ ዶክተር ሚስት የዚያን ጠበል ተዓምር ትሰማና ወደዚያ
ቦታ በቅርቡ ትሄዳለች፡፡ እዚያ ስትሄድ በመተትም ይሁን በደንቃራ የምትጠረጥረውን ሰው ስም አስመዝግበህ ለጸሎት ፕሮግራም
አጋልጠህ ነው እምትመጣውና ሴትዮዋም ይህንን አድርጋ ትመለሳለች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አጅሬ - ለምን የውሸት ስም አልሰጠውም
- አጅሬ ጫላ ወደዚያ ቦታ ይጠራል፡፡ ወደድህም ጠላህም ሰው ሳይሆን የሠራኸው ወንጀልና ኃጢያት ነው እያክለበለበ እሚወስድህ እንጂ የሰውም ይሁን የጽሑፍ ቀላጤ ባለህበት
አይመጣልህም፡፡ ጫላ ባላወቀው ሁኔታ መኪናውን አስነስቶ ወደዚያ ሥፍራ ሲሄድ በላዩ ላይ የተከሰተው የአጋንንት መንፈስ
የዶክተሩን ማስገደል ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም ገመናዎቹን ዘክዝኮ ይናገራል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሀብታም ለመሆን ባደረገው ምትሃታዊ
ጥረት አንድ ወይፈንና አንድ ጥቁር አህያ በሠራው ፎቅ
ሥር ከነነፍሳቸው መቅበሩን ያጋልጣል፡፡ ይህ ሰው - ጫላ -
ከዚያን ቅጽበት ጀምሮ ጤናማ ኅሊናውን ይስታል፡፡ የሄደባት ግሩም የመስክ መኪናም እዚያው እጠበሉ ሥፍራ አደባባይ ላይ እንደተገተረች
ናት፤ በዚህ መልክ ተትተው የቀሩ ሌሎች መኪኖችም አሉ - ሄዶ በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እሱ አሁን ወደ ቤቱ ተመልሶ የፈጣሪን
ፍርድም በዚያው እንዲጠባበቅ ተነግሮት በብረት ታስሮ እየተጠበቀ ነው - ከዚህ ያውጣን፡፡ ይህ እኔ ራሴ ያረጋገጥሁት ነገር
ነው፡፡ ሌሎች አሁን እዚህ ልናገራቸው የማይገባኝ ብዙ ሀገራዊ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዚያ ቦታ የማትሰሙት ነገር የለም - ትንግርት
ነው፡፡ በብዙ ሺህ የሚገመተው በተለይ ወጣቱ እንዲያ በግዝት ሰንሰለት እየታሰረ በአጋንንት መንፈስ የዛር ዳንኪራ ሲረግጥ ስታዩ
በእርግጥም የሰይጣን ዋና መሥሪያ ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሆነ ልታምኑ ትገደዳላችሁ፡፡ ዋናው የአጋንንት ማደሪያዎችም ባለፈው
‹መረጃ› ጠቅሼ እንደጠቆምኩት ብፁዕ ወርኩስ ማለቴ ወ‹ቅዱስ› አባታችን አባ ገብረ መድኅን በሃይማኖቱ ክንፍ፤ ክቡር ጠቅላይ
ሚኒስትራችን ብፃይ መለስ ዜናዊ በፖለቲካው ክንፍ፤ በግማሽ የሳዑዲ ተወላጁ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን በንግዱ ዘርፍ ከሉሲፈር የተሾሙልን
የወቅቱ የዲያቢሎስ ወኪሎች ናቸው - አራት ነጥብ፡፡ እኔ በመሠረቱ ፈራጅም ዳኛም አይደለሁም፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ መልካም
ሰዎችንም ሆነ ክፉ ሰዎችን በሥራቸው ታውቋቸዋላችሁ ስለሚል ከተግባራቸው ተነስቼ እነዚህ ሰዎች የዚህ ወይም የዚያ ወኪሎች ናቸው
ብል የምችልና ኃጢያቴም ለሥርየት የሚበቃ ይመስለኛል፡፡ ይቃጠላሉ፤ ይነዳሉ፤ ወዮላቸው… አላልኩም፡፡ ያ የእግዜር ጉዳይ እንጂ
የኔ አይደለም፡፡ ከዚያ ዓይነቱ ፍርድ እኔ ራሴም ስለማምለጤ እርግጠኛ ባልሆንኩበት ሁኔታ በሰው ላይ ልፈርድ አልቃጣም፡፡
ደግሞም ፈጣሪ የቅጣት ሳይሆን የምሕረት አባት በመሆኑ እነ አባ ጳውሎስና እነ አቶ መለስም ተጸጽተው በሥራቸው የሚገኘውን
ያማሰኑትን መንጋ ይቅርታ ጠይቀው ንስሃ ቢገቡ ምሕረትን የማያገኙበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ሳዖል እኮ ክርስቶስን ከማሳደድ ተመልሶ
ነው በጳውሎስነቱ የእግዚአብሔርን መንግሥት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ያገለገለው፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር የሚሳነው
ነገር የለምና እነዚህን አሳዳጆቻችንን ፈጣሪ በምሕረት ዐይኑ ቢጎበኛቸውና ከዲያቢሎስ ግዛት ቢያወጣቸው የኛም የመከራ የዕዳ
ደብዳቤ ይቀደድና ለነጻነታችን ትንሣኤ የምናደርገው ትግልም ይቀልልን ነበር፡፡
በመምህራን ላይ ባነሳሁት ጉዳይ ትንሽ ነገር ላክል፡፡ የወያኔው ስግስግ
መምህራን ወሬ እንዲያቀብሉት በምሥጢር ሰብስቦ ይጠይቃቸዋል አሉ፡፡ አድማውን እነማን እየመሩት እንደሆነና እነሱን በመመንጠር
ከሥራ ለማስወጣት ወይም ሌላ እርምጃ ለመውሰድ፡፡ ያኔ እነዚህ የወያኔ ዕንባ ጠባቂ መምህራን ‹እንዴ፣ ይህንንማ አናደርግም፤ የኢኮኖሚ ችግሩ እኮ እኛንም እየጎዳን
ነው፤ ስለዚህ ለኛም መብት የሚጥሩ ወንድሞችና እህቶቻችንን እንዴት አሳልፈን እንሰጣችኋለን?› በማለት አሳፍረዋቸዋል፡፡ ይህ
የጥንቱን ኢትዮጵያዊነት - የዓላማ ጽናትን፣ አድር ባይነትን መጸየፍን፣ ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆምን - የሚያሳይ ለዘመናችን አዲስ
ጅማሮ ስለሆነ የሚያስደስት ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ አንጀት ለማያጠረቃ ዳረጎትና ወንዝ ለማያሻግር ዘውጋዊ ጽንፈኝነት ብለን
አንድነታችንን የሚያናጋ ለተጨማሪ ዓመታት ጭቆናም የሚያጋልጠንን ተግባር መፈጸም የለብንም፡፡ ሰው መሆን የሚጀመረው ከዚህ ነው
- በጥቅም ሰውን አሳልፎ ካለመሸጥ፡፡ የዚህ ዓይነት መተባበር ከመጣ ነጻነታችን በጣም ቅርብ ነው፡፡ በዚህ ላይ መምህራኑ
የመብት ጥያቄ ሲያቀርቡ መከፋፈል የለባቸውም፡፡ የምንታዘባቸው ነገሮች አሉ - ብዙው ከሥራ ሲቀር አንዳንዱ ይሄድና ‹እኔ ለሥራየ
ቀናኢ ነኝ› በሚል ይጎናበሳል፡፡ ይህ ጠባያችን እየለያየ ያስመታናል፡፡ሁሉም አንድ ከሆነ የማናሳካው የመብት ጥያቄ የለምና
በዚህ ረገድ በፍርሀትም ሆነ በሌላ ምክንያት መምህራንም ሆኑ ሌሎች ሠራተኞች መለያየት የለብንም፡፡ የሞራልና የሃይማኖት ሰበዝ
የሌለው ወሮበላው ወያኔም ሆነ ማንኛውም ሌላ መንግሥት ኅብረትን አይወዱም፡፡ ይፈሩታል፡፡ እናም በመተባበር መብታችንን
እናስከብራለን ፤ ባለመተባበርና በመለያየት ስቃያችንን እናራዝማለን፡፡ ስለዚህ የሚጠቅመንን ብንመርጥ ይበልጥ እንጠቀማለን እንጂ
አንጎዳበትም፡፡
ታስታውሱ
እንደሆነ ይህ ዮዲት ጉዲታዊና አህመድ ግራኛዊ የአጥፊዎች መንግሥት ሥልጣን በያዘ ሰሞን የባንክ ቤት ሠራተኞች አድማ መትተው
ነበር፡፡ ያኔ ወያኔ በምትካቸው ሠራተኛ ለመቅጠር ማስታወቂያ ሲያወጣ በሚያሣፍር ሁኔታ ለመመዝገብ የተሠለፈው ሕዝብ ዙሪያ
ጥምጥም ነበር፡፡ እንደኢትዮጵያዊነትም ሆነ እንደሰው ከዚህ በላይ አሳፋሪ ነገር የለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ኅሊናን እሚሰቀጥጥ ዕኩይ
ተግባር ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ዓለም ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ሰው እንዴት በወንድምና እህቶቹ ጉሮሮ
ላይ ይቆማል? ሃይማኖትን፣ ይሉኝታን፣ ባህልን… ምን በላው ይባላል? ነግ በኔ እንዴት ይረሳል? በእውነቱ ብልግና ነበር፡፡
አሁንም ወያኔ ክፍተት የሚሞሉ ‹መምህራን›ን በበቂ ሁኔታ አዘጋጅቻለሁ እያለ ነው፡፡ ውሸቱን ነው፡፡ መምህር ዕንቁላል
አይደለም- መምህር የዶሮ ጫጩት አይደለም - በዶሮ መኖና ፉርሽካ በአንድ ቀን አዳር ተጥሎና በ21 ቀናት ተፈልፍሎ ወደሥራ
የሚሠማራ፡፡ ወያኔ በ‹ማስቦካት› ሙያ የተካነ በመሆኑ ለማስፈራራት እንጂ እንኳንስ ተጠባባቂ መምህራን ሊኖሩት ያሉትም በቂ እንዳልሆኑ
እዬተነገረ ነው፡፡ ከየት አባታቸው ሊያመጡ? መምህር ቀልድ ነው? ወይንስ በሌሎች መስኮች ለምሳሌ በፖለቲካ ፓርቲ ጥፍጠፋው እንደለመደው
ቦዘኔና ዱርየውን ሰብስቦ ሳልቫጅ እያለበሰ ‹እንዲያስተምሩ› ሊልካቸው ነው? ለነገሩ ትምህርት ከሞተ ሰነበተ አይደል? ወያኔ
ለትምህርት ሽፋን ካልሆነ ለትምህርት ጥራት ሲጨነቅ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አያውቅም፡፡ ያም ቢሆን ለታይታና ለብድርና ዕርዳታ
ማግኛ ይመስለኛል፡፡
ወያኔ
ሚሊዮኔር ገበሬ መፍጠሩን ሰምታችኋል አይደል? እሱም ውሸት ነው፡፡ በቀደም አንዱ ገበሬ ነው የነገረኝ፡፡ አጭበርባሪው ወያኔ የጎበዙን ገበሬ ማሣ ለሥራ ጉዳይ ለተወሰነ አጭር ጊዜ እፈልገዋለሁ በሚል
ለባለቤቱ አምስት መቶ ብር ይከፍለውና ሳተና ጋዜጠኞቹን ያሰማራል፡፡ የተዘጋጀ ‹ሀብታም› ገበሬ በዚያ ማሣ ውስጥ
እንዲንጎራደድና ሚሊዮነር መሆኑን ቀድሞ ባጠናው የፋርስ ድራማ ስክሪፕት መሠረት በኩራት እንዲናገር ይደረጋል፡፡ ለዚህም ውሸቱ
አምስት መቶ ብር ይከፈለዋል፡፡ በዚያ ተመሳሳይ ማሣ አሥርና አሥራ አምስት ‹ሚሊዮኔር› ገበሬዎች በዬተራ ፊልም ይቀረጹና
ድራማውን በግሩም ሁኔታ የተወኑት ተመርጠው እጅ እጅ በሚለው ኢቲቪ ለፈረደብን ምሥኪን ዜጎች ይቀርባል፡፡ በዚህ መልክ ከቀረቡ
ገበሬዎች የአንድኛው ልጅ ፕሮግራሙን ከተመለከተች በኋላ፤ ‹እንዴ
አባዬ፣ ሁለት ሚሊዮን ብርማ ካለህ ለምን ወደከተማ ሄደን አንድ ነገር አንሠራም? እዚህ አገር ቤት ገጠር ውስጥ ምን እንሠራለን?...›
ብላ ካለችበት በስልክ ስትጠይቀው ‹ተይኝ ልጄ፣ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ እኔ እንኳንስ ሚሊዮን ሊኖረኝ ምሣ በልቼ ራት የማልደግም
ድሃ ነኝ፡፡ ምሥጢሩን ስንገናኝ እነግርሻለሁ› ማለቱን ከሁነኛ ሰው ሰምቻለሁ፡፡ እውነተኛ ታሪክ ነው እምነግራችሁ፡፡ ወያኔ እኮ
የማይሠራው ድራማ የለም፡፡ ያመረተውን አነስተኛ ምርት በግዳጅ በውድ ዋጋ ለሚሸጥለት የማዳበሪያ ዕዳ የሚከፍል ገበሬ፣
ያመረተውን ሸጦ ዕጥፍ ድርብ ለተቆለለበት የግብር ዕዳ ክፍያ የሚያውል ገበሬ፣ በሰው ሠራሹ የኑሮ ውድነት እንደማንኛውም
የሀገሪቱ ጭቁን ዜጋ ክፉኛ የሚንገበገብ ገበሬ … በጥቅሉ የዕለት ጉርሱን መሸፈን ያልቻለ ምሥኪን አርሶ አደር በወያኔ ቤተ
ሙከራ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በምን ተዓምር ሚሊዮኔር ሊሆን ይችላል? ‹ቴነር›ና ‹ፊፍቲየር›ም በሆነ(ባለ10 እና ባለ50 ብር
ጌታ ማለቴ ነው - እኔስ አዲስ ሀብታም መፍጠር አልችልም?)፡፡
ኢንቬስተሮችን
በርዕሴ አንስቻለሁ፡፡ ትንሽ ምክር ቢጤ ልወርውር፡፡ ሰው በተፈጥሮው የተዳላ ኑሮን ይፈልጋል፡፡ ፍላጎትን የመቆጣጠርና ልቅ
የመተው ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ገንዘብንና ሀብትን የማይሻ የለም - እነዚህን ምድራዊ ፀጋዎች ጠግቦ ይህችን ምድር የተሰናበተና
በአንድ እጅ ጣቶች ከሚቆጠሩ ኔልሰን ማንዴላንና ማህተመ ጋንዲን ከመሰሉ እጅግ ጥቂቶች በስተቀር የ‹በቃኝ›ን ምሥጢር የተረዳ
ሰው ስለመኖሩም አላውቅም፡፡፡፡ የዚህች ምድር መገለጫም ይሄው የሀብትና ሥልጣን የወሲብም ጣጣ ነውና፡፡ ጽድቅና ኩነኔ በኋላ
እሚመጡ ናቸው - በቅጡ ማሰብ ሲጀመር፡፡ በአፍላ ዕድሜ ግን ብዙውን ጊዜ ገንዘብ ለመሰብሰብ መሯሯጥ ነው እሚታየው፡፡ በዚህ
ሂደት እሚስተዋሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በቅርቡ በሄድኩበት ጠበል የታዘብኩትም ይህንኑ ነው፡፡ ብዙ በሽተኞች ኢንቬስተሮችና
ገንዘብን አለቅጥ የሚሹ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ናቸው፡፡ ለገንዘብ ሲሉ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ አንዱና እኔ በነበርኩበት
የጸሎት ወቅት የተፈወሰ ወጣት ኢንቬስተር ለምሳሌ የማይገባበት ቀዳዳ ሁሉ እየገባ ነበር 18 ባንኮችን ያጨናነቀ ገንዘብ ሊያከማች
የቻለው፡፡ ይህ ጉዳይ በሺዎች ምዕመናን ፊት የተገለጠ ስለሆነ እውነትነቱን አትጠራጠሩ፡፡ ግን ወጣቱ ምን ተጠቀመ? ሄዶ
የሠራውን ሁሉ ለፈለፈ በሰንሰለትም ታስሮ ለወራት ከተጠበለ በኋላ ገና በቀደምለት በወርቅ ካከበረው ከሰውነት ተራ ግን ካወጣው ርኩስ
መንፈስ ተላቀቀ፡፡ በዚያ ቦታና በሌሎችም እውነተኛ ጠበሎች አካባቢ የማትሰሙት ጉድ የለም ብያችሁ የለም? አዎ፣ ብዙ እሚዘገንን
ነገር ታዳምጣላችሁ፡፡ ሰው ሁሉ በገንዘብ ፍቅር አበደ እንዴ ትላላችሁ፡፡ እርስ በርስ መተባተብና ተቆላልፎ የሰይጣን መጫወቻ
መሆን ምንድነው ትርፉ ታዲያ? ከአንድ እንጀራ የበለጠ ለማይበላው ይህን ያህል ኅሊናን ስቶ በድግምትና በጥንቆላ መለከፍን ምን
አመጣው? የሰይጣን አሽከር ሆኖ በወገን ሕይወት መቀለድ መቅረት አለበት፡፡ በኃጢያት መጥቶ ከሚያበሰና ጮማ በጤና ተበልቶ ንጹሕ
እንቅልፍ የሚያስገኝ ጎመን ይሻላል፡፡ ስለሆነም ውድ ኢንቬስተሮቻችን - በአንዳንዶቻችሁ ላይ እየታየ ያለው ገንዘብ የማከማቻ
ሥልት እጅግ አጸያፊና ወንጀልና ኃጢያት የሞላው ነውና በቶሎ ተስተካከሉ፡፡ በኃጢያት የመጣ ገንዘብ መቅኖ የለውም፡፡ ይዞ ጠፊ
ነው፡፡ በልማትና ኢንቬስትመንት ሰበብ ከወያኔ ጋር እዬተሸረካችሁ ሕዝቡንም መኖሪያና የእርሻ ቦታ አታሳጡት፡፡ አንድ በጣም
የማውቀው ሰው በዚሁ መንገድ በሰለበው ገንዘብ ትልቅ ሕንፃ ሠርቶ ገና አላባውን ሳይበላ ነው ዐይቶ ብቻ የሄደው፡፡ የርሱ
ቢጠየዎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ያከማቻሉ ግን አይበሉትም፤ ቤት ይሠራሉ ግን አይኖሩበትም፡፡ ቀድሞ በትንቢት ተነግሯል፡፡
አስተዋይና ልባም ጠፋ እንጂ - ይህም ቀድሞ ተተንብይዋል፡፡ ስለዚህ ለአላፊና ጠፊ ብልጭልጭ ነገር ለምን ከፈጣሪም ከሰውም ጋር
እንጣላለን? ለምንስ የጸሎት ዱላ እናዘጋጃለን? የጸሎትና የዕንባ በትር ደግሞ ሲመታ እንጂ ሲወረወር አይታይም - እናም ልንከላከለው ወይም ልናመልጠው አይቻለንም፡፡ እርግጥ ነው ሂዜ
ሊወስድ ይችላል፡፡ ያም ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ይቅርብን፡፡ በአፍንጫችንም ይውጣ፡፡ እናም ሕንፃም ስትሠሩ ሆነ አንዳች የልማት
ዕቅድ ስታከናውኑ ለሠይጣን ግብር ይሆን ዘንድ የምትታዘዙትን የሰውና የእንስሳ ጭዳ አትቀበሉ፡፡ የተገተረውን ሕንፃና ወፍጮ በእውን
አንስተን ብንመለከት ወይም በምናባችን ብንቃኝ ብዙ የሰው ልጅ አፅሞችን እናገኛለን፡፡ ስንት ሺህ ዓመት ለመኖር ይሆን ሰውን
ያህል በአርአያ ሥላሤ የተፈጠረ አምሳያችንን ገድለን ሀብት ለማፍራት የምንቋምጠውና በተግባር የምንፈጽመው? የለም፣ የለም - ከገባንበት አረንቋ እንመለስ! ጆሮ ያለው
ይስማ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰይጣናዊ ድርጊት ለሚፈጽም ሰው ፈጣሪ አመዛዛኝ ኅሊናና አስተዋይ ልቦና ይስጠው፡፡ ከዚህ የነጻን ነን ለምንልም በአቋማችን ጸንተን በድህነታችን
የመንግሥቱ ወራሶች እንድንሆን ያድርገን፡፡ አሜን ማለት ማንን ገደለ - ‹አሜን!!› አትሉም?
ሌሎች
ዜጎችም ወደየኅሊናችን እንመለስና ከዚህ ሀገር ምድሩን ከወረረው የጥንቆላና የድግምት ጠንቅ እንውጣ፡፡ በውነቱ በየጠንቋዩና
በየደብተራው ደጅ እሚርመሰመሰውን ሕዝብ ስትመለከቱ የኢትዮጵያን የነጻነት ምፅዓት ልትጠራጠሩ ትችላላችሁ፡፡ ምን ነካን ብላችሁም
ትጨነቃላችሁ፡፡ ከማን ጋርስ ሆነን ነው ሀገርን የምናለማው ብላችሁ ታስባላችሁ፤ በውስጣዊ የባዶነት ስሜትም ትተክዛላችሁ፡፡ ሰው
አቅሉን ስቶ ወንድም ወንድሙን እህት እህቷን በገንዘብ ምክንያት ሲከዳዱና በየዱበርቲው፣ በየአባይ ጠንቋዩ፣ በየሥራ ሥር በጣሹ፣
በየኮከብ ቆጣሪው፣ በየመጣፍ ገላጩ፣ በየ ሥኒ ተመልካቹ፣ በየ አውሊያ ቤቱ … ደጅ ሲጠና ስታዩ ልባችሁ በሀዘን ይሰበራል፡፡ ‹ከዚህ ባዕድ አምልኮታዊ ልክፍት መቼ ይሆን
የምንላቀቀውና ዘመናዊ ሰዎች የምንሆነው?› ብላችሁ በተደጋጋሚ ራሳችሁን ልትጠይቁ ትገደዳላችሁ - ለጥያቄያችሁ ግን መልስ
የላችሁም - ያም ይብስ ያስጨንቃችኋል፡፡ ብዙ ጉድ አለብን፡፡ ወዮ ለኛ፡፡ ማይምነትና የአጋንንት መንፈስ ከላይ ከቤተ
መንግሥትና ከቤተ አምልኮቶቻችን ጀምሮ ክፉኛ እየተጫወቱብን ናቸው - ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ፡፡ መቼም ለእግዜር የሚሳነው
ነገር ስለሌለ በምሕረቱ ሲዳብሰን ከተጀቦንንበት ጨለማና ከተጣለብን ሟርትና ደንቃራ እንላቀቅ እንደሆነ እንጂ አሁን ተስፋን
እሚያመነምኑ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ቢሆንም ተስፋ አንቁረጥ - ነገም ሌላ ቀን ነው ይባላልና፡፡
በነገራችን
ላይ በውጭ ሀገር ያላችሁ ዜጎቻችን ከፍተኛ ተስፋዎቻችን ናችሁና ከዚህ ከምለው ነገር አንጻር ራሳችሁን ጠብቃችሁ፣ ገንቢ
ዕውቀትና ልምድ ቀስማችሁ በትንሣኤያችን ወቅት ለሕዝባችሁ ቤዛ እንድትሆኑት ከወዲሁ እንዳቅሚቲ ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ፡፡
ማይምነት ከላይ የጠቃቀስኩትን ሰይጣናዊ ነገሮች በዋናነት ጨምሮ ለብዙ መጥፎ ነገሮች እንደሚዳርግ የታመነ ነው፡፡ መማርና ዲግሪ
መያዝ በራሱ ምንም እንዳልሆነ ቢታወቅም በትምህርት ላይ የግል ጥረትና የተፈጥሮ አስተዋይነት ሲታከልበት ውጤታማ መሆኑ አያጠራጥርምና
በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ ያላችሁ ወገኖች በትንሣኤያችን ወቅት የየወቅቱ
ደናቁርት አገዛዞች ላገዛዛቸው እንዲያመቻቸው በማይምነት ተብትበው
በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚያላቅጡትን ይህን ሕዝብ ወደ ብርሃን ለማውጣት ብዙ ይጠበቅባችኋል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ራሳችሁ ወደ
ብርሃን ውጡ፡፡ ራሱ በጨለማ ውስጥ የሚዳክር ‹ምሁር› ሌሎችን ወደብርሃን ማውጣት አይችልም፡፡ … አሣራችን ብዙ ነው፡፡
ኢትዮጵያን እንደገና ለመሥራት የሚያስፈልገንን ግብኣት ሳስበው እውነቴን ነው ራሴን ያመኛል፡፡ ብቻ ዲያስፖራው አደራውን በመጪው
ጊዜ እንዳያሳፍረን፤ ከርሱ ነው ብዙ እምንጠብቅ - በመንፈስም
በሥጋም፡፡ እኛንስ በቁማችን ገድለውናል፡፡ ለዚህ ያበቁንን እግዜር ይይላቸው፡፡
እግዚኣብሔር
ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ መምጣቱና ቤቱን ማጽዳቱ፣ አጽድቶም በአዲስ ማዕጠንት እንደገና ማጠኑ አይቀርምና ያን በጉጉት
የምንጠብቀውን ወርቃማ ዘመን በቶሎ ያምጣልን፡፡ አሜን፡፡፡
No comments:
Post a Comment